Commentary: በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ የተሰጠ ግላዊ ሀሳብ

ሐምሌ 6 ቀን 2018 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ቁጥር 7 ስብሰባን ተከትሎ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ ሌሎች ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው የብድር ጣሪያን ሙሉ ለሙሉ ማንሳቱንና የፖሊሲ ወለድ ምጣኔውን ከ15% ወደ 16% ማሳደጉን ገልጿል።

ባጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን (NBE) የቅርብ ጊዜ የገንዘብ ፖሊሲ ጥቅል ስልታዊ በሆነ መንገድ ትክክለኛና አስፈላጊ መዋቅራዊ ማሻሻያ አድርጌ እመለከተዋለሁ፤ ነገር ግን ይህ ማሻሻያ ጉልህ የሆኑ አጭር ጊዜ trade-offs የሚያስከትል ነው። የፖሊሲው ለውጥ ከአስተዳደራዊ ቁጥጥሮች ወደ ገበያ መር የገንዘብ አስተዳደር መሸጋገርን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህም ከብዙዎቹ በታዳጊ ኢኮኖሚ ላይ ካሉ አገራት አቅጣጫ ጋር የሚስማማ ነው። ይሁን እንጂ የዚህ ሽግግር ስኬት የሚወሰነው በራሱ በፖሊሲው መውጣት  ላይ ሳይሆን፣ በዋናነት በአፈጻጸሙ፣ ከበጀት ፖሊሲ (fiscal policy) ጋር ባለው ቅንጅት እና በንግድ ባንኮች ባህሪ ላይ ይሆናል።

በጎ መዋቅራዊ ሽግግር

በጣም ወሳኙ ውሳኔ የብድር ጣሪያውን ማንሳት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ብሔራዊ ባንኩ ቀጥተኛ የሆኑ የብድር መጠን ቁጥጥሮችን ለመተው መወሰኑ እና በምትኩ እንደ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔ፣ የተጠባባቂ ገንዘብ ፍላጎቶች፣ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ (Treasury bill) ሥራዎች እና የፈሳሽ ገንዘብ አስተዳደር (liquidity management) ባሉ ቀጥተኛ ባልሆኑ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ላይ ለመደገፍ መምረጡ ነው።

ይህ የኢትዮጵያን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መሠረታዊ የሆነ ዘመናዊነትን ያሳያል። የብድር ጣሪያዎች በአጠቃላይ እንደ ጊዜያዊ የችግር ጊዜ መሣሪያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። የብድር መጠን በመገደብ የዋጋ ግሽበትን ሊቀንሱ ቢችሉም፣ የብድር አከፋፈልን ያዛባሉ፣ የፋይናንስ ፈጠራን ያዳክማሉ፣ እና ባንኮች በንግድ እሳቤዎች ላይ ተመስርተው ብድር የመስጠት አቅማቸውን ይቀንሳሉ።

የብድር ጣሪያውን ማንሳት፣ ብሔራዊ ባንኩ የፋይናንስ ሥርዓቱ ገበያ መር የሆኑ መሣሪያዎች ገንዘብን(liquidity)እና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ቀዳሚውን ሚና ሊረከቡ የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረሱን ማመኑን ያሳያል።

ፖሊሲው አሁንምጥብቅ ነው

አንዳንድ ታዛቢዎች የብድር ጣሪያውን ማንሳት የገንዘብ ፖሊሲ ማላላት (monetary easing) አድርገው ይተረጉሙታል። እኔ ግን በዚህ አልስማማም።

የፖሊሲው ወለድ ምጣኔ በተመሳሳይ ጊዜ ከ15% ወደ 16% መጨመሩ፣ ከተወሰኑ የተጠባባቂ ገንዘብ ፍላጎቶች መተግበር እና ከቀጣይ liquidity አስተዳደር ጋር ተዳምሮ፣ ብሔራዊ ባንኩ አሁንም ገዳቢ (የጠበቀ) የገንዘብ ፖሊሲ አቋምን እያስቀጠለ መሆኑን ያሳያል። ዓላማው አሁንም የዋጋ ግሽበትን መቀነስ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ግን ብድር ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈል መፍቀድ ነው።

በእውነቱ፣ ብሔራዊ ባንኩ ማስፈፀሚያውን ነው የቀየረው እንጂ ዓላማውን አይደለም።

የአጭር ጊዜ ፈተናዎች

ሽግግሩ ያለ ዋጋ (ወጪ) የሚመጣ አይደለም።

ከፍተኛ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔዎች የባንኮችን የገንዘብ ምንጭ ወጪ (funding costs) የሚጨምሩ ሲሆን፣ ለንግድ ተቋማት የሚሰጠውን የብድር ወለድ መጠን ሊያሳድጉ ይችላሉ። በተመሳሳይ ጊዜ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ (Treasury bills) እና የማዕከላዊ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ አገልግሎቶች (deposit facilities) ይበልጥ ማራኪ እየሆኑ ይመጣሉ፤ ይህም ባንኮች ያላቸውን ፈሳሽ ገንዘብ ከፍተኛ ድርሻ ከግል ብድር ይልቅ ዝቅተኛ ስጋት ወዳለባቸው የመንግሥት ዋስትና ሰነዶች ላይ እንዲመድቡ ሊያበረታታ ይችላል።

ይህ በሰፊው የሚከሰት ከሆነ፣ በተለይም ቀድሞውኑ የፋይናንስ እጥረት ላጋጠማቸው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ በተወሰነ ደረጃ የግል ኢንቨስትመንትን የማጨናነቅ (crowding out) ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።

ይህ ስጋት እውነተኛ ቢሆንም፣ የማይቀር ግን አይደለም። የሚወሰነው በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ነው

  1. በመንግሥት እና በግል ብድር ትርፋማነት መካከል ባለው ልዩነት
  2. በባንኮች መካከል ባለው ውድድር፣
  3. በግል የብድር ፍላጎት ፍጥነት፣
  4. እና በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ- liquidity አስተዳደር ላይ።

የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ተስፋዎች

የዋጋ ግሽበቱ እየቀነሰ ከቀጠለ እና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ ላይ ያለው እምነት እየጠነከረ ከሄደ፣ ፖሊሲው በርካታ የረጅም ጊዜ ጥቅሞችን ሊያስገኝ ይችላል፦

  1. ይበልጥ ውጤታማ የሆነ የብድር አከፋፈል
  2. ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ተወዳዳሪነት፣
  3. የተሻሻለ የገንዘብ ፖሊሲ ስርጭት (transmission)፣
  4. ጠንካራ የባለሀብቶች እምነት፣
  5. የጠለቁ (የሰፉ) የፋይናንስ ገበያዎች፣እና
  6. በአስተዳደራዊ ጣልቃገብነቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ።

እነዚህ ውጤቶች የኢትዮጵያን ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ይደግፋሉ።

ለስኬት ወሳኙ ሁኔታዎች

አሁን ያለው ትልቁ ፈተና የፖሊሲ ቅንጅት (policy coordination) ነው።

የገንዘብ ፖሊሲ ብቻውን ቀጣይነት ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ሊያመጣ አይችልም። ውጤታማነቱ የሚወሰነው በማሟያ የበጀት ዲሲፕሊን፣ በጥንቃቄ በተሞላበት የመንግሥት ብድር፣ በቀጣይ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች እና በንግድ አካባቢ መሻሻሎች ላይ ነው።

የበጀት ፖሊሲው ዲሲፕሊን አሀን ባለት ከቀጠለ እና የመንግሥት ብድር የባንክ ዘርፉን ፈሳሽ ገንዘብ ከልክ በላይ ካልመጠጠው፣ አዲሱ ማዕቀፍ የመሳካት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በተቃራኒው የመንግሥት የፋይናንስ ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ ከቀጠለ እና የሰነድ መዋዕለ ንዋይ (Treasury bill)  የባንኮችን ሀብት ባልተመጣጠነ መልኩ መቀማታቸውን ከቀጠሉ፣ የግል ዘርፍ የብድር ዕድገት ተዳክሞ ሊቀጥል ይችላል።

ማጠቃለይ

ሁኔታውን አመዛዝኜ ስመለከተው፣ የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ለውጥ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ትክክለኛ ስልታዊ አቅጣጫ መሆኑን እገመግማለሁ። በወለድ ምጣኔ ላይ ወደተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መሸጋገር ከአለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ጋር የሚስማማ ከመሆኑም በላይ ለረጅም ጊዜ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ጠንካራ መሠረት ይሰጣል።

ይሁን እንጂ ይህ ፖሊሲ ለሁሉም ዘርፎች በአፋጣኝ ጥቅም የሚያስገኝ አይደለም። በአጭር ጊዜ ውስጥ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ የብድር ወጪ ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ ባንኮችም ብድርን በማስፋፋት ረገድ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይችላሉ። በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ ግን አፈጻጸሙ እምነት የሚጣልበት ከሆነና በበጀት ዲሲፕሊን ከተደገፈ፣ ማሻሻያዎቹ የፋይናንስ መካከለኛነትን (financial intermediation) ውጤታማነት ለማሻሻል፣ የዋጋ ግሽበት ቁጥጥርን ለማጠናከር እና ይበልጥ ጠንካራና ገበያ ተኮር የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት ለመፍጠር አቅም አላቸው።

ባጭሩ የፖሊሲ ለውጡን «በስልታዊ መንገድ ተገቢ ነገር ግን በአሠራር ረገድ ፈታኝ» በማለት እገልጸዋለሁ። የመጨረሻው ስኬት የሚወሰነው በራሱ በብድር ጣሪያው መነሳት ላይ ሳይሆን፣ ብሔራዊ ባንኩ liquidityን ምን ያህል ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደሚያስተዳድር፣ የንግድ ባንኮች እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ፣ እና በሽግግሩ ወቅት የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲዎች ምን ያህል ተጣጥመው እንደሚቀጥሉ ላይ ነው።

Samson Tsedeke



We use essential and analytics cookies to improve your experience and site performance. By using this website, you agree to our Privacy Policy and cookie use.